FDRE Ministry of Agriculture

ለግብርናው ዘርፍ መዘመን የትብብር ስራዎችን ማጠናከር!

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27/ 2018 (ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይልማ ሲሳይ ከብራዚል የወጭ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ኤጄንሲ ፕሬዚዳንት ላውደሚር ሙለር ከተመራ ልዑክ ጋር በሁለቱ ሃገራት በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎችና ቀጣይ ትብብሮች ላይ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያና የብራዚል ግንኙነት ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የትብብር ዘርፎች እየተተገበረ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን ሰፊ አቅም ለመጠቀም ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነች ሲሆን ይህን ይበልጥ ለማሳደግ ብራዚል በዘርፉ ካላት የካበተ ልምድ ተሞክሮዎችን መቀመር የትብብሩ የትኩረት መስክ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በቡና ምርታማነት፣ ጥራት፣ ማቀነባበርና እሴት ሰንሰለት፣ በግብርና ምርምርና ቴክኖሎጂ ልውውጥ፣ በግብርና ግብዓት አቅርቦትና ሜካናይዜሽን፣ ውጤታማ የመስኖ ቴክኖሎጂ ሽግግግር፣ የአፈር ለምነትና አያያዝ፣ የኩታ-ገጠም እርሻ፣ በእንስሳት እርባታ እና በሌሎችም ጉዳዮች ትብብርን ማጠናከር ይገባል፡፡

ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የብራዚል የወጭ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ኤጄንሲ ለዘርፉ እድገት በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ይሰራል፡፡

ኤጄንሲው የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ፣ የግብርና ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በማስተዋወቅ፣ የግብርና ንግድ እና የእሴት ሰንሰለት እድሎችን በማበረታታት የአግሪ-ቢዝነስ ኩባንያዎችን ከዓለምአቀፍ አጋሮች ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡

ለዚህም በአፍሪካ የመጀመሪያውን ቢሮ በኢትዮጵያ የከፈተ ሲሆን የግል ባለሃብቱን በዘርፉ በማሳተፍ ለኢትዮጵያ ግብርና መዘመን ትልቅ ድርሻ እንደሚያበረክትም ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በግብርና እና ኢንቨስትመንት ሰፊ አቅም ያላት መሆኑ እንዲሁም በኢትዮጵያ በኩል የአፍሪካ ሃገራትን በቀላሉ ማግኘት ስለሚያስች ኤጄንሲው ቢሮውን በአዲስ አበባ መክፈት እንዳስቻላቸው በውይይቱ ተነስቷል፡፡