ዲላ፣ ግንቦት 11/2018 (ግብርና ሚኒስቴር)በግብርና ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ የነፍሳት ፊዚዮሎጂና ሥነ-ምህዳር ማዕከል አዘጋጅነት የዓለም የንብ ቀን ምክንያት በማድረግ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንብ ሀብት ልማት ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተከሂዷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አዝዝ አያሌው የንብ ተፈጥሮአዊ ተልዕኮ ማር ማምረት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅ የእፅዋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡

የውይይት መድረኩ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሔ ሀሳቦች የሚመነጩበት፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ነጥቦች የሚነሱበት፣ ለንብ ሀብት ልማትና ለስራ እድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታ ለመፈጠር የሚያስችሉ ሀሳቦች የሚቀርቡበት መሆኑን መሪ ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዲዮ ዞን አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የንብ ሀብት አቅም በመኖሩ በሁሉም ዞኖች ማር እንደሚመረት ጠቅሰው፣ ለዓብነት በጌዲዮ ዞን ብቻ በአመት ከ3500 እስከ 4 ሺህ ቶን ማር እንደሚመረት ተናግረዋል።

በዚህም ለ60ሺህ አርሶ አደሮችና ወጣቶቸ የገቢ ምንጭ በመሆን በዓመት እስከ 7 መቶ ሚሊዮን ብር ገቢ እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ያለ ንብ አግሮ ኢኮሎጂውን ማስተካከል አንችልም ያሉት ኃላፊው፣ በግብርናው ዘርፍ ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ የንብ ሀብት ልማት ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪ በውይይት መድረኩ ለንቦች መደረግ ስለሚገባው ጥበቃና ጥንቃቄ፣ ንቦች የአከባቢን ሚዛን ለማስጠበቅ እፀዋትን በማዳቀል ያላቸው ጠቀሜታ፣ ማህበረሰብ አቀፍ የኬሚካል አጠቃቀም ስርዓት እና መሰል ጉዳዮች ላይ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ማለቶ
ፎቶግራፈር፡- ጌታቸው ምትኩ
