FDRE Ministry of Agriculture

ለበርካቶች የስራ ዕድል የፈጠረው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ህብረት ስራ ዩኒየን

ሆሳዕና፣ ነሀሴ 24/2018 (ግብርና ሚኒስቴር) መንግስት የወተትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዘርፉ ለተሰማሩ ማህበራትና ዩኒየኖች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ለዚህም አንዱ ማሳያ ሊቻ የወተት ማቀነባበሪ ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ህብረት ስራ ዩኒየን ሲሆን ዩኒየኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ይገኛል፡፡

ዩኒየኑ በቀን 1 ሺህ 500 ሊትር ወተት በላይ ወተት ከአባል ማህበራት እየተረከበ የታሸገ ትኩስ ወተት፣ እርጎ፣ ክሬም፣ አጓት፣ አይብ እና ቅቤ በማቀነባበር ለአካባቢው ማህበረሰብ እና ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረበ ነው፡፡

የወተት ማቀነባበሪያ ዩኒየኑ ለ43 ቋሚ ለ100 ሰዎች ደግሞ ጊዚያዊ የስራ ዕድልም ፈጥሯል፡፡

የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ ኤርሚያስ ሽፈራው ዩኒየኑ በ2017 ዓ.ም ወተት ማቀነባበር እንደጀመረ አስታውሶ በስሩም 83 መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት እና 106,081 አርሶ አደር አባላት ያሉ መሆኑን ገልጿል፡፡

ዩኒየኑ የሚያቀነባብረውን ወተት መጠኑን እና ጥራቱን በመጨመር እንዲሁም የዱቄት ወተት በማምረት ምርቱን ለአለም ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡

የክልሉ መንግስት እንዲሁም ዞኑ እና ወረዳው ዩኒየኑን ለማሳደግ ላበረከቱት አስተዋፅዖ ምስጋና ያቀረበው ስራ አስኪያጁ፤ ድጋፍ እና ክትትሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *