የዝናብ ጥገኝነትን ግርግዳ የናደው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ ሲቀረፅ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለመተካት ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርት የማድረግ ግብ ተጥሎ ነበር ወደ ስራ የተገባው፡፡
በዚህም ግቦቹን እውን ከማድረጉ ባሻገር በአጠቃላይ በስንዴ ልማቱ ሀገራችን የአፍሪካ ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏታል፡፡

በየዓመቱ እስከ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማውጣት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባለፈ ዛሬ ላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ልማቱ በትኩረት በመሰራቱ በስንዴ ምርትና ምርታማነት ስርነቀል ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡት ውጤቶችም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
በ2011 ዓ.ም በ3 ሺህ 502 ሄክታር መሬት ላይ ተጀምሮ የተገኘው ምርት 100 ሺህ ኩንታል ሲሆን በጊዜው በዝናብ ወቅት የተመረተው ስንዴ 61.7 ሚሊዮን ኩንታል ነበር፡፡

በ2012/13 ምርት ዘመን አጠቃላይ የስንዴ ምርት 70.2 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን በ2016/17 ምርት ዘመን 290.8 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ ተችሏል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ የማምረት አቅም ላይ የተደረሰ ሲሆን የስንዴ አማካይ ምርታማነትን በሄክታር ወደ 36 ኩንታል በማሳደግ ሀገራችን በስንዴ ልማት ተምሳሌትነት የአፍሪካ ሀገራት ልምድ መቅሰሚያ መሆን ችላለች፡፡

ለስንዴ ልማቱ ስኬት የኩታገጠም እርሻ አሰራርን በአግባቡ መተግበር በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ከሱ ጋር ተያይዞ የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም እጅግ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ዛሬ ላይ 27 ሺህ የደረሰው የትራክተር ቁጥር ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ባለሀብቶችን በማሳተፍ ሰፋፊ የመስኖ ልማትን መተግበርና ከአመራሮች ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በቁርጠኝነት በመስራታቸው ይህ አኩሪ ስኬት ተመዝግቧል፡፡
በቀጣይም ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዘጋጅ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ
