ሀቼሪ (Hatchery) ማለት ከወላጅ ወይም ከቅድመ ወላጅ ዶሮዎች የሚገኙ ለመፈልፈል የተዘጋጁ እንቁላሎችን በተቀመጠ የሙቀት፣ የእርጥበት እና የአየር ዝውውር ሁኔታ ውስጥ በማቆየት በ21 ቀናት ውስጥ የዶሮ ጫጩት እንዲፈለፈሉ የሚያደርግ ማሽን ወይም ስርዓት ነው።
ሀቼሪ በዘመናዊ የዶሮ ልማት ሂደት ውስጥ አስፈላጊ መሠረተ-ልማት ሲሆን ጤናማ፣ ጥራት ያለውና በብዛት የተሻሻለ የዶር ዝርያ ጫጩት ለማምረት ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ሀቼሪ በዶሮ ሀብት ልማት ላይ ያለው አስተዋፅዖ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን በተለይም የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን በብዛት፣ በፍጥነት እና በተደራጀ መንገድ ለአርሶና አርብቶ አደሮች፣ ለወጣቶች፣ ለባለሀብቶች እንዲሁም ዶሮ ለሚያረቡ ሁሉ ለማቅረብ ያግዛል። ይህም የዶሮ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ሀቼሪ (Hatchery) በሚከተሉት ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል፦
⏩የተሻሻለ የዶሮ ጫጩት ዝርያ አቅርቦትን ማሳደግ
⏩ የዶሮ ስጋ እና የእንቁላል ምርት እንዲጨምር ማገዝ
⏩ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር
በተጨማሪም ሀቼሪ ለእንቁላል ምርታማነት ዕድገት ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ሲሆን በዚህም የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎች ከአካባቢ ዶሮዎች ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ የእንቁላል ምርት ይሰጣሉ።
ሀቼሪ በአንድ ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ ጫጩቶችን ለማስፈልፍል ስለሚያስችል የእነዚህ የተሻሻሉ ዝርያዎች ስርጭት በፍጥነት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡

ሀቸሪ የእንቁላል ምርት መጠን እንዲጨምር ከማድረጉም ባሻገር በገበያ የእንቁላል አቅርቦት እንዲሻሻልና የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር ያደርጋል፣ የስርዓተ-ምግብ ደህንነት እንዲረጋገጥና እንዲጨምር ያግዛል፡፡
ከሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ አንፃር የዶሮ ሀብት ልማት ከዋና ዋና የትኩረት መስኮች አንዱ ሲሆን ይህ ኢኒሼቲቭ የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል፣ የእንስሳት ምርትን ለማሳደግና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
በዚህም ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ዋና ማነቆ ሆኖ የቆየው የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያ አቅርቦት እጥረት ሲሆን ሀቼሪ (Hatchery) ይህን ችግር በመፍታት የተሻሻሉ የዶሮ ጫጩቶችን በብዛት እና በጥራት ለማቅረብ ያስችላል።
በመሆኑም ሀቼሪ ለሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ስኬታማነት ትልቅ ድርሻ ያለው ሲሆን የሚከተሉትን አስተዋፅዖዎች ያበረክታል፡-
⏩የዶሮ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ
⏩የምግብና ሥነ-ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል
⏩የማህበረሰብ ገቢን ለማሻሻል
⏩የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ
ግብርና ሚኒስቴር የዶሮ ሃብት ልማትን ለማሳደግ ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ 76 ሺህ 800 እንቁላሎችን መታቀፍ የሚችል አራት ዘመናዊ የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ማሽኖችን “ሀቼሪ” Hatchery በሞጆ፣ በቦንጋ፣ በኮምቦልቻ እና በሀዋሳ ከተሞች ለሚገኙ የዶሮ ማባዣ ማዕከላት ድጋፍ በማድረግ የማዕከላቱን የምርታማነት አቅም ብሎም የጫጩት ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ እየሰራ ነው፡፡

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በሀገራችን እየጨመረ የመጣውን የዶሮ፣ የሥጋና የዕንቁላል ፍላጎት ለሟላት የሀቼሪ (Hatchery) ማሽን አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ የዶሮ እና የዕንቁላል ሀብት ልማት ሥራውን በዘመናዊ መንገድ በመስራት ምርትና ምርተማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነታችን ማረጋገጥ ለነገ የማይተው ቁልፍ ተግባር ነው፡፡
አዘጋጅ፡- ሰለሞን ደምሰው
